የ2000 ምርጫና የህዝብ ተሳትፎ

ሚያዝያ 10፣ 2000 ዓ/ም

ከመስፍን ሺፈራው

በሀገራችን የሚካሄዱ ምርጫዎች  የህዝቡ ሉዓላዊነት መገለጫ ናቸው። ማንኛውም በሕዝብ የሚካሄድ ምርጫ ፍላጎቱንና ጥቅሙን በማስከበር በኩል በትክክል ይወክለኛል የሚለውን የሚመርጥበት አይወክለኝም የሚለውን ደግሞ ድምፅ የመስጠት ስልጣኑን በመጠቀም ወደ ፖለቲካ ስልጣን እንዳይወጣ የሚወሰንበት መሣሪያ ነው።

የአንድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች አንዱ የህዝቡ ተሳትፎ ነው። በአንድ ሀገር በሚካሄድ ምርጫ የህዝብ ተሳትፎ መኖር የራሱ ትርጉም አለው። የህዝቡ በምርጫ ውስጥ መሳተፍ የዲሞክራሲ መብቱን መጠቀሙን ከማሳየት በላይ ህዝቡ በስርዓቱ ላይ ያለው አመኔታና የባለቤትነት ስሜት ይወሰናል ።

 በምርጫ የህዝብ ተሳትፎ ሲባል ህዝቡ ከምርጫው በፊት የቀረቡለት አማራጮች ላይ ግልፅ መሆንን፣ ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፀም አስፈላጊው ድጋፍ ማድረግን፣ ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ እንዲካሄድ የበኩሉን ድርሻ ማበርከትን፣ በመራጮች ምዝገባ ወቅት በነቂስ ወጥቶ መመዝገብንና በምርጫው እለትም ይመሩኛል የሚሉትን ፓርቲዎች ወይም ግለሰቦች መምረጥን  ከሁሉ በላይ ደግሞ በምርጫ  ላይ የባለቤትነት ስሜት ማሳደርን ይሆናል።

በተጨማሪም ህዝቡ በምርጫው እንዲሳተፍ የሚጋብዙ የተለያዩ አማራጮች መኖርና ህዝቡ በምርጫ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ሰላማዊ ሁኔታ መፈጠሩ የህዝቡን የምርጫ ተሳትፎ ለማሳደግ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ያጠቃልላል። ከዚህ አንፃር ከ1983 ወዲህ በኢትዮጵያ የተካሄዱት ምርጫዎች ከፍተኛ ሕዝብ የተሳተፈባቸው መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። የተቀሩትን ትተን የ2000 ዓም ምርጫ ማየቱ በቂ ነው።

 በዚህ ዓመት በሚካሄደው ምርጫ መምረጥ ከሚገባው ሕዝብ 26 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ ለመራጭነት መመዝገቡን ይፋ ተደርጓል። ከዚህ ውስጥ ባለፈው ሚያዝያ 5 ቀን 2000 በተካሄደው የአካበቢና የማሟያ  ምርጫ ከ90 በመቶ በላይ ሕዝብ ድምፅ መስጠቱን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል። ይህ አሃዝ በማናቸውም መለኪያ ሲታይ ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ መኖሩን ያመላክታል። በአንዳንድ በሰለጠኑና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ረጅም ልምድ ካላቸው ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው።

ሌላው ከሕዝብ ተሳትፎ ጋር የሚያየዘው ህዝቡ ለምርጫው በስጠው ትኩረት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች  ጨዋነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመምረጡ ተግባር ላይ መሳተፉ ነው። ለዚህም  ራሱ መራጩ ህዝብ፣ የምርጫ ታዛቢዎችና የፀጥታ አስከባሪና የምርጫ ቦርድ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። 

በምርጫው ሕዝብ በስፋት ሊመዘገብና ሊመረጥ የቻለው በዋነኛነት ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ የሚፈልገውን እንዲመርጥ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ነው። ከዚህ አንፃር ተጠቃሹ ሕዝቡ የፈለገውን እንዲመርጥ የፓለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ዘመቻና ዓላማቸውን የማስተዋወቅ ሥራ በመንግሥት ሚዲያዎች እንዲያካሄዱ መደረጉ ነው።

በሀገሪቱ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ በምርጫው ለመሳተፍ የፈለጉ ሁሉም ፓርቲዎች አለን የሚሏቸውን ዓላማዎች፣ አቋሞችና እምነቶች በነፃና በእኩልነት ለህዝቡ ግልፅ አድርገዋል። የተለያዩ የሕዝብ መድረኮችም በመፍጠርና በሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች አቋሞቻቸውን ለህዝቡ አሳውቀዋል። ይሄንን በማድረጋቸውም ከየትኛውም ወገን ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አላደረሰባቸውም። ይልቁንም አንዳንዶቹ የምርጫ ስነምግባር ደንብ ከሚፈቅደው ውጭ የሌላውን ፓርቲ የሚያንቋሽሽ ተግባር በቅስቀሳቸው ወቅት እስከመጠቀም ሄደዋል።

ህዝቡ የምርጫን ፋይዳ ተገንዝቦ በምርጫው በስፋት እንዲሳተፍ ሰፊ ሥራ መስራቱና በምርጫ ቦርድ በኩል ከሌሎች ጊዜያት የተሻለ ዝግጅት መደረጉ ሕዝቡ ተሳትፎ ማደግ የራሱ አስተዋፅኦ አድርጓል።

ከሁሉም በላይ መንግሥት ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት ህዝቡ በምርጫ ሂደተ እንዲሳተፍ አመቺ ሁኔታ መፍጠሩ፣ የምርጫው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መካሄድ በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲኖር አስፈላጊ መሆኑን በማመን ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ እንዲፈፀም ቁርጠኝነት ማሳየቱ፣ህዝቡ ያለምንም ስጋት በምርጫ ጣቢያዎቸ በመገኘት መምረጥ እንዲችል የተጠናከር የጸጥታ ስራ መሰራቱ ለህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆን ጉልህ ሚና አበርክቷል።

ምርጫው በከፍተኛ ህዝብ ተሳትፎ የተካሄደ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ህጋዊና ህገወጥ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝቡ በምርጫው እንዳይሳተፍ ምንም ዓይነት ሙከራ አላደረጉም ማለት አይደለም።ይልቁንም ምርጫው ዴሞክራሲያዊ አይሆንም፣ አባሎቻችን ታስረውብናል፣ ወከባ ተፈፅሞብናል በሚል ሽፋን ህዝቡ በምርጫው ላይ እምነት እንዳይኖረው ሰፊ ጥረት አድርዋል። አንዳንዶቹም የራሳቸውን የውስጥ ችግር መሸፈኛ ለማድረግ ሲጠቀሙበት ተስተውሏል። አንዳንድ የውጪ ሚዲያዎችም ይህንን የተቃዋሚዎች መሰረተቢስ ሮሮ በማስተገባት በምርጫው ብዙህዝብ አይሳተፍም የሚል ሀሳብ ሲያሰራጩ  ከርመዋል።

በእርግጥ ህዝቡ ለእነዚህ የማደናገሪያ እንቅስቃሴዎች አልተበገረም። ከዚህ በላይ በ1997ቱ ምርጫ የነበረውን ጠባሳ ወደጎን በመተው በስፋት ወጥቶ ወኪሎቹን መርጧል። ይህም ሊያደርግ የቻለው በምርጫው ሂደት ላይ አመኔታ በማሳደሩ ነው። ስለሆነም ሕዝቡ ባለፈው እሁድ ያሳየው ከፍተኛ ተሳትፎ በሚመጣው እሁድ በመድገም በዴሞክራሲያዊ መብቱ መጠቀም ይኖርበታል። በሀገራችን የዴሞክራዊያዊ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ተገቢውን ድርሻ ተወጣ የሚባለው ይህንን ሲፈፅም ነውና።